ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 95 ቢሊዮን ዶላር ተገኘ

ሚያዚያ 21/2014 (ዋልታ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ገቢ 2 ነጥብ 95 ቢሊዮን ዶላር ማገኘቷን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

ገቢው ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ20 ነጥብ 3 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ ገልፀዋል።

የወጪ ንግድ ገቢው አፈፃፀም ድርሻ በዘርፍ ደረጃ ሲታይ ግብርና 69% ፣ ኢንዱስትሪ16% እና ማዕድን 15 በመቶ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ተመላክቷል።

የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀም ግመገማ በተካሄደበት መድረክ ላይም የወጭ የንግድንና የሀገር ውስጥ የምርት አቅርቦትና ስርጭትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደቆየ ተገልጿል።

በዚህም የንግድና ኢንቨስትመንት ፍቃድ ለመስጠት 31 ቀናት ይፈጅ የነበረውን ሂደት ወደ 5 ቀናት ለማውረድ ተችሏል ነው የተባለው።

መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን አቅርቦትና ስርጭት ለማሻሻልም እንደ ዘይት፣ ስኳርና ሩዝ የመሳሰሉ ሸቀጦችን ከውጭ በማስገባት አቅርቦትና ፍላጎቱን ለማጣጣም ተሰርቷል ተብሏል።

ከቀጠናዊ ትስስር ጋር በተያያዘም የተለያዩ የአለም አቀፍና የክፍለ አህጉር ስምምነትና የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች አየተከናወኑ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በቁጥጥርና ክትትል ስራ ረገድም የሀገር ሀብትን ከህገወጥ ነጋዴዎች የመታደግ ስራ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ ነው የተመላከተው።

በዘርፍ ያለውን ጤናማ፣ ፍትሀዊና ሚዛናዊ የንግድ እንቅስቃሴ ፍትሃዊ ለማድረግ ህዝቡና ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን በቅንጅት ሊወጡ እንደሚገባ መልዕክት ተላልፏል።

 

በደምሰው በነበሩ