ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ የመጡትን የሀሳብ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለምክክር መቀራረብ አስፈላጊ ነው – ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ምስፍን አረአያ

ግንቦት 21/2016 (አዲስ ዋልታ) ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ የመጡትን የሀሳብ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለምክክር መቀራረብ አስፈላጊ እንደሆነ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 7 ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምክክር ምዕራፍ መድረክ እያካሄደ ይገኛል ፡፡

በዚሁ ወቅት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደገለጹት ኮሚሽኑ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ኃላፊነቱን በመወጣት ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መሻገሩን ገልፀዋል ።



ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊዎች በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ እንዲንፀባረቅላቸው የሚፈልጓቸውን አጀንዳዎች እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ በመውረድ ያላግባቡ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት በውይይት እየተፈቱ የጋራ ሀገር ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲሳካ ሁሉም ሚናውን መወጣት ይጠበቅበታልም ብለዋል።

በግዛቸው ግርማዬ