ሰኔ 17/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከአሌክሳንደር ፑሽኪን አደባባይ ተነስቶ በጎፋ ማዞሪያ ወደ ጎተራ ማሳለጫ የሚወስደው ዋና የመንገድ ክፍል ለትራፊክ እንቅስቃሴ ክፍት መደረጉን አስታውቋል፡፡
ከፑሽኪን አደባባይ ወደ ጎተራ ማሳለጫ የሚወስደው መንገድ 320 ሜትር ርዝመት ያለው የዋሻ ስራን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመጠናቀቁ ለትራፊክ ክፍት ሆኗል ነው የተባለው፡፡
የፕሮጀክቱ ቀሪ የግንባታ ስራዎችም በተያዘላቸው ጊዜ መሰረት እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጸው ባለስልጣኑ፣ የመንገዱ በዚህ ደረጃ ለትራፊክ ክፍት መሆን በቄራ እና አካባቢው የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀርፍ አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ 3 ነጥብ 8 ኪ.ሜ ርዝመት እና 45 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፣ በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ቻይና ፈርስት ሀይ ወይ ኢንጂነሪንግ የተባለ የስራ ተቋራጭ መስከረም 2012 ዓ.ም የግንባታ ስራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሰክሪታሪያት መረጃ ያመለክታል፡፡