ኬንያ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ያወጀውን የተናጥል የተኩስ አቁም እንደምትደግፍ ገለፀች

ሰኔ 24/2013 (ዋልታ) – ኬንያ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ያወጀውን የተናጥል የተኩስ አቁም እንደምትደግፍ ገለፀች፡፡

በኬንያ የኢትዮጵያ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ሲራጅ ራሺድ በኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ እና የአፍሪካ ሕብረት ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት መንግስት በትግራይ ክልል ያወጀው የተናጥል የተኩስ አቁምን ጨምሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚመለከትም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር መቀጠል ያለበት መሆኑንና የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊያን መፈታት ያለበት መሆኑን ገልጸውላቸዋል።

የኬንያ መንግስትም አፍሪካ አስተባባሪነት የሚካሄደውን የሶስትዮሽ ድርድር እንዲደግፉ ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና ኬንያ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ያወጀውን የተናጥል የተኩስ አቁም እንደምትደግፍ ገልጸው፣ ኬንያ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚካሄደውን የሶስትዮሽ ድርድርም እንደምትደግፍ ተናግረዋል።

የሁለትዮሽ ጉዳዮችን አጠናክረው በጋራ ለመስራት ፍላጎታቸው መሆኑን በተለይ በቅርብ ጊዜ በኢኮኖሚ ሁለቱን ሀገራት ለማስተሳሰር እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በማድነቅ ህዝቡን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በተቀናጀ መልክ መስራት ጠቃሚ እንደሆነ መግለፃቸውን በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡