ክለቦች ከሊግ ውድድር ባሻገር በየደረጃው ላሉት ክለቦችም ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

ታኅሣሥ 24/2014 (ዋልታ) ሁሉም የአገሪቱ ክለቦች ከሊግ ውድድር ፉክክር ባሻገር በየደረጃው ላሉት ክለቦችም ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገለፀ።
ፌዴሬሽኑ በአርባ ምንጭ ከተማ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ሲሆን በዓመቱ ስኬቶቹና ተግዳሮቶቹ ላይ መክሯል።
በዚህም ፌዴሬሽኑ በዓመቱ የሁለቱ ፆታ ብሔራዊ ቡድኖችን ጨምሮ በሁሉም የዕድሜ እርከን 8 ብሔራዊ ቡድኖችን ማዋቀሩን ገልጿል።
የፕሪሚየር ሊግ ውድድር እራሱን ችሎ እንዲቋቋም ማድረጉን የገለፀው ፌዴሬሽኑ በፋይናንስ የተጠናከረ ተቋም ማድረግ፣ የአካዳሚ ፕሮጀክት መመሥረት መቻሉንና እና የመረጃ አያያዝና ስርጭቱን ዘመናዊ በማድረግ ላይ እገኛለሁ ብሏል፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ እንደተናገሩት ክለቦች ከሊግ ውድድር ፉክክር በዘለለ በሁሉም እርከን የሚገኙ የአዳጊ ክለቦቻቸው ላይ ትኩረት በመስጠት እግር ኳሱን ማሳደግ ይገባቸዋል።
ሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከቀጣይ ዓመት ጀምረው የሴት ቡድን መያዝ እንደሚገባቸው በመግለፅ ይህንን ያላደረገ ክለብ በካፍ ውድድር ላይ እንማይሳተፍ ገልፀዋል ሲል የዘገበው ደሬቴድ ነው።