ክልሉ ከ4 ሺሕ 500 በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 4 ሺሕ 552 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ።
የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ4 ሺሕ በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ40 በላይ የሚሆኑት በፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው የነበሩ እንደሆኑ እና 210 በነፍስ ግድያ የተጠረጠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
አሁን ላይ ሕገ ወጦችን ለመያዝ ከሚደረግ ሥራ ውጭ ክልሉ አስተማማኝ ሰላም ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊው መንግሥት የክልሉን ዘላቂ ሰላም የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
ትክክለኛውን የፋኖ ስም የማይወክሉ፣ በፋኖ ስም ተደራጅተው በሕዝብ ላይ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ቡድኖችን መንግሥት እንደማይታገስም ገልጸዋል።
ትክክለኛ የፋኖ አባላትን በመንግሥት መዋቅር ሥር በማድረግ እንዲሠሩ እየተደረገ እንደሆነ ኃላፊው መጠቆማቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡