ኮሚሽኑ ከንግዱ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው

ኅዳር 7/2015 (ዋልታ) የፌዴራል ሥነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከንግዱ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ቋሚ ኮሚቴዎች የሥነምግባርና ፀረ ሙስና አስፈፃሚዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የፌዴራል ሥነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ለሙስና እና ሙሰኞች እጅ መስጠት እንደማያስፈልግ ገልጸው ሙስናን ለመዋጋት ከነበረው የተለየ የህግ ማስከበር ስራ በተግባር የሚታይበት አካሄድ መኖር አለበት ብለዋል።

ሙሰኞችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ መንግስት አሁን ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የዚህ የትኩረት አቅጣጫ ተሳታፊ መሆን የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሌላው በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አይሻ ያህያ በንግድ ዘረፉ ውስጥ የሚስተዋለውን የሙስና ተግባር መዋጋት የጋራ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የምክክር መድረኩ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን ከ180 በላይ የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ሚልኪያስ አዱኛ (ከአዳማ)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW