ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ግንቦት 12/2014 (ዋልታ) እውቁ ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ) በተወለደ በ57 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ዶክሌ በሚለው ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ወንድወሰን ባጋጠመው የልብ ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ትናንት በአሜሪካ ዋሽንግተን ሜድስታር ሆስፒታል ውስጥ ማረፉን የሙያ አጋሩ አርቲስት ቴዎድሮስ ለገሰ ገልጿል።
“ዶክሌ ቅንና ታዛዥ ባለሙያ ነበረ” ያለው አርቲስት ቴዎድሮስ ኢትዮጵያውያን ኮሜዲያን ዶክሌን ሲረዳው ቢቆይም ለሁለተኛ ጊዜ ታሞ ሆስፒታል ገብቶ ህክምና እንዲያገኝ ቢደረግም ህይወቱን ማትረፍ እንዳልተቻለ መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ኮሜዲያን ዶክሌ በመድሐኒአለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል።
የእሱንም ሆነ የቤተሰቡን ህይወት ለመምራት በመካኒክነት ትምህርት ቀስሞ ሲሰራ የቆየ ሲሆን በኋላ ላይ የጥበቡን ዓለም በመቀላቀል በኮሜዲ ዘርፍ አንቱታን ያተረፈባቸውን በርካታ አይረሴ ሥራዎችን ሰርቷል።
በስታንድ አፕ ኮሜዲ እጅግ በርካታ አጫጭር ቁምነገር አዘል ቀልዶችን ያቀረበው ኮሜዲያን ዶክሌ በሙሉ ጊዜ የፊልም ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ዕውቅናና ዝናን ያተረፈ ነበረ።
ለአብነትም የራስ አሽከር የሚለው ታሪክ ቀመስ ፊልም ላይ የላቀ የትወና ብቃት እንዳለ ማስመስከር ችሏል።
በሥራ አጋጣሚ ከስምንት አመታት በፊት ወደ አሜሪካ አቅንቶ ኑሮውን በዚያው አድርጎ የነበረው ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ) ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበር።