ኮቪድ-19 መከሰት ለኤችአይቪ/ኤድስ የሚሰጠውን ትኩረት እንዲቀንስ ማድረጉ ተገለጸ

ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ትኩረታቸውን ለኮቪድ-19 በማድረጋቸው ለኤችአይቪ/ኤድስ የሚሰጠውን ትኩረት እንዲቀንስ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የኤችአይቪ/ኤድስ ቀን በአለም ለ34ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ33ኛ ጊዜ “ኤችአይቪ/ኤድስ ለመግታት አለም አቀፍ ትብበር እና የጋራ ሀላፊነት” በሚል መርህ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተከብሯል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኤችአይቪ/ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ሲስተር  ፈለቀች አንዳርጌ መዲናዋ ከጋምቤላ ክልል በመቀጠል ከፍተኛ የስርጭት መጠን አስመስግባለች ብለዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል 4 ነጥብ 8 በመቶ የስርጭት መጠን ሲመዘገብ፤ በአዲስ አበባ 3 ነጥብ 2 በመቶ መመዝገቡን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

በዚህም 30 በመቶ የስርጭት መጠን ከ15 እስከ 24 እድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ወጣቶች በመሆናቸው ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ669 ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው እንዳላቸውና ከእነዚህም ከ114 ሺህ በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ እንደሚገኙም ዳይሬክተሯ አመላክተዋል፡፡

ላለፉት 20 አመታት ለኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት ለመቀነስ በተደረገው ጥረት በቫይረሱ የሚከሰተውን ሞት 52 በመቶ መቀነስ የተቻለ ሲሆን፣ በቫይረሱ አዲስ የመያዝ መጠን 49 በመቶ መቀነስ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

(በነስረዲን ኑሩ)