ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን መቀበል ጀመረ

መጋቢት 5/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከፍተኛ ውድመት ተፈፅሞበት ተዘግቶ የቆየው የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት ተማሪዎቹን መቀበል መጀመሩን አስታውቋል።
ተማሪዎቹ ከጧት ጀምረው ወደ ግቢ በመግባት ላይ መሆናቸውን የጠቀሰው ዩኒቨርሲቲው የተቋሙ የጥበቃና ደኅንነት ሰራተኞችም በግቢው በር ላይ አስፈላጊውን የፍተሻ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጿል።
ቀደም ሲል ተማሪዎች መጋቢት 5 እና 6 ቀን 2014 ዓ.ም በቅጥር ግቢው በመገኘት እንዲመዘገቡ ጥሪ ያደረገው ዩኒቨርሲቲው በተጠቀሱት ቀናት ወልዲያ ከተማ ለሚገቡ ተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ያመቻቸ መሆኑን አመልክቷል።
ተማሪዎች በተጠቀሱት ቀናት ከጧቱ 2:30 ጀምሮ በመናኸሪያ፣ በፒያሳ፣ በአዳጎና ጎንደር በር ፌርማታዎች ላይ በመገኘት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ መሆኑንም አስታውቋል።