ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን ጥር 29 ያስመርቃል

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጥር 29 ለ2ኛ ጊዜ በ40 የትምህርት ክፍሎች ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 785 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ድግሪ እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው 2ሺህ 510 ተማሪዎችን በመደበኛ መርሃግብር፣ 275 ተማሪዎችን ደግሞ በኤክስቴንሽን መርኃግብር ያሰለጠናቸው መሆናቸውን ገልጿል፡፡

በመደበኛ መርሃግብር ከሚያስመርቃቸው ተማሪዎች መካከል 1ሺህ 685 ወንድ ሲሆኑ፣ 625 ደግሞ ሴት ተማሪዎች ናቸው፡፡

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሱልጣን ሙሀመድ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የወጣውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል ህግን በመተግበር የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘሮችን ከማዘጋጀት ጀምሮ የሙቀት መለኪያ ቴርሞሜትሮችን በመግዛት እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ተማሪዎች እንዲጠቀሙ በማድረግ ሰፊ ስራ እንደተሰራ ገልጸዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ እና የተረጋጋ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ የጋራ መግባባት ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት እንዲሁም የተማሪ መማክርት አባላት እና ኮሚቴ በማዋቀር እየሰራ መሆኑንም ዶ/ር ሱልጣን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅርበት የሚሰራ ኮሚቴ አዋቅሮ የሚፈጠሩ ችግሮችን ከመሰረቱ በመፍታት የትምህርት ስርዓቱን ሰላማዊ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ነሐሴ 14፣ 2012 ዓ.ም በሁለተኛ ድግሪ መርሃግብር ያሰለጠናቸውን 46 ወንድ እና 41 ሴት በአጠቃላይ 87 ተማሪዎችን ማስመረቁ ይታወሳል፡፡

(በብርሃኑ አበራ)