ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ይጀምራል

የካቲት 1/2014 (ዋልታ) የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የሚጀምር መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አበበ ግርማ (ዶ/ር) ገለጹ።

በአሸባሪው ትሕነግ ውድመትና ዘረፋ የተፈፀመበት ዩኒቨርሲቲው የመልሶ ጥገና ስራ በማከናወን ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የማታ ተማሪዎችን ተቀብሎ ዳግም የመማር ማስተማር ስራውን ይጀምራል።

የመጀመሪያ አመትና ተመራቂ ተማሪዎችን ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በመቀበል ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአሸባሪው ትሕነግ ከ6 ቢሊዩን ብር በላይ ግምት ያለው ሃብት ዘረፋና ውድመት የደረሰበት መሆኑን አስታውሰው የተለያዩ ጥረቶች ተደርገው ለዳግም የመማር ማስተማር ሂደት ዝግጁ ሆኗል ብለዋል።

ከሌሎች ዘጠኝ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ባገኘው ድጋፍ በመጀመሪያው ምዕራፍ ዳግም ስራ ለመጀመር የሚያስችለው ደረጃ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

ዩኒቨርሲቲውን ስራ ለማስጀመር በተደረገው ርብርብ የተማሪዎች መኝታ፣ የመማሪያ ክፍሎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለማሟላት መቻሉን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከመንግስት፣ ከበጎ አድራጊዎችና ከቀድሞ ተማሪዎች ጋር በመሆን ዩኒቨርሲቲውን የማሟላት እቅድ መያዙን ተናግረዋል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ያለምንም ስጋት ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በአሸባሪው ትሕነግ ዘረፋና ውድመት የተፈፀመባቸው የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተማሪዎችን በመቀበል ዳግም ስራ የሚጀምሩ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።