ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ሚያዝያ 21/2014 (ዋልታ) ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በመሥራት  የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ዛሬ ከዋናው መስሪያ ቤት እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ጋር  ተወያይቷል።

በሀገር ውስጥ፣ በቀጣናው፣ በአኅጉር እና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተፈጠሩ ሁነቶች ያስከተሉት ተዛማች ተፅዕኖ እና ያ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የፈጠረውን ጫና ለመቀልበስ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ፐብሊክ እና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተከወኑ ሥራዎች ያስገኙት ውጤት፣ የነበሩ ጠንካራ ጎኖች እና በቀጣይ ሊስተካከሉ የሚገባቸውን መሰናክሎች በማጠቃለል ቀርቧል።

ባለፉት 9 ወራት ሥርዓታዊ ለውጥ ለማምጣት እና ሀገርን ለማፍረስ የተቀናጀ የውስጥ እና የውጭ ዘመቻ ተከፍቶ እንደነበር በውይይቱ ተነስቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ብዙ ፈተናዎች ውስጥ መሠረቷን ሳትለቅ አጋጥሟት የነበረውን ከባድ ፈተና አልፋለች ነው ያሉት።

በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራትም በዋናው መሥሪያ ቤት፣ በተጠሪ ተቋማት እና ሚሲዮኖች የተናበበ ሥራ በመስራት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ መጓዝ ይገባል ነው ያሉት።

በችግር ውስጥ እየታለፈም ተቋማዊ ለውጥ እና መዋቅራዊ ማሻሻያውን በስኬት ማጠናቀቃችን ትልቅ ውጤት ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የዓለም ጂኦ ፖለቲካ በተለያዩ ጎራዎች እያለፈ መሆኑን በማንሳት ኢትዮጵያ እያንዳንዱን ርምጃዋን ከብሔራዊ ጥቅሟ አኳያ እየመዘነች ምክንያታዊ እና የተሰላ ስትራቴጂካዊ አካሄድ እየተከተለች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአኅጉሩ ደረጃ ያላትን ሥፍራ አስጠብቃ እየተጓዘች ሲሆን ለስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ውስጣዊ ጥንካሬ መሠረት በመሆኑ በዚህ ረገድ በቀጣይም በሀገራችን ያሉ ችግሮችን መፍታት ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ሀገራዊ የለውጥ ማሻሻያውን መሠረት  በማድረግ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ራሱን በመፈተሽ ባለፉት  9 ወራት  ስኬታማ ማሻሻያ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ ሚኒስትር ዴኤታዋ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ናቸው።

ማሻሻያው ዲፕሎማቱ በምዘና እንዲያልፍ እና አዳዲስ የሚሲዮን አደረጃጀቶች ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ የተተገበሩበት እንደነበርም አንስተዋል።

አደረጃጀቱ እና ማሻሻያው ወጭ ቆጣቢ እና ተደራሽነታችንን ያሰፋ ሆኖ ተከውኗል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የተቀናጀውን ዘመቻ በመቀልበስ ረገድ ዳያስፖራው ተሳትፎሞ ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ያብራሩት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እንድሪስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ስኬታማ በነበረው የመጀመሪያው ምዕራፍ  ታላቁ ጉዞ ወደ ሀገርቤት ዳያስፖራው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ከ1 ነጥብ 4 ብር በላይ ገቢ ማድረጉም ጠቅሰዋል።

ከሰራተኞች አስተያየት እና ጥያቄዎች ቀርበው ለጥያቄዎቹ ከመድረኩ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን አስተያየቶቹ ለቀጣይ ሥራዎች እንደ መልካም ግብዓትነት ይወሰዳሉ ነው የተባለው።

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW