ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአፍሪካ ህብረት ከቻይና አምባሳደር ሊዮ ዩሺ ጋር ተወያዩ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአፍሪካ ህብረት የቻይና አምባሳደር ሊዮ ዩሺ ጋር በአዲስ አበባ ስለሚገነቡት የአፍሪካ ህብረት ፕሮጀክቶች እና ተያያዥ የትብብር ስራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄዱ።

ምክትል ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ በውይይታቸው የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ /ሲ.ዲ.ሲ/ ዋና መስሪያ ቤትን ዕውን የማድረግ የትብብር አቅጣጫ ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ማዕከል ከተማ መሆኗን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባዋ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ስራዎችና ፕሮጀክቶችን በትብብር መስራንት እንቀጥላለን ብለዋል።

የአፍሪካ መንደር ፕሮጀክት እና የሲ.ዲ.ሲ አፍሪካ ዋና መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ እንዲገነቡ በማድረግ ረገድ ላደረጉት አስተዋጽኦም በከተማው አስተዳደር ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል /ሲዲሲ/ ዋና መስሪያ ቤት የመሠረተ ድንጋይ ባለፈው ሳምንት የተቀመጠ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የሚገነባው የማዕከሉ ህንጻ ወጪው በቻይና መንግስት የሚሸፈን መሆኑ ተነግሯል፡፡