ወደ ቻይና በሚላኩ ምርቶች ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ውይይት ተካሄደ

በመጋቢት 9/2014 (ዋልታ) ወደ ቻይና በሚላኩ የወጪ ምርቶች ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ የበይነ-መረብ ውይይት ተካሄደ።

የቻይና ጠቅላላ ጉሙሩክ አስተዳደር በቅርብ ተግባራዊ ደንብ መሰረት ከሁሉም የዓለም አገራት ወደ ቻይና የሚገቡ የግብርና እና ምግብ-ነክ ምርቶች የተቀመጠውን ዘርፈ ብዙ መስፈርቶችን አልፈው በቻይና ጉሙሩክ አስተዳደር በኩል በተዘረገው አዲስ የኦንላይን መመዝገቢያ ቋት ላይ መመዝገብ እንዳለባቸው ይደነግጋል።

በዚህ መሰረት የቻይና መንግሥት ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል የማያሟሉ ድርጅቶች ከመብዛታቸው ጋር ተያይዞ ለከፍተኛ ችግርና እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸው ተጠቅሷል።

በውይይቱ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና ከተለያዩ የላኪ ድርጅቶች ማኅበራት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች የተሳተፉ ሲሆን የአዲሱ ህግ ድንጋጌዎችና በላኪ ድርጅቶች ላይ እየፈጠረ ያለው ተፅዕኖ በስፋት ተነስቷል።

ችግሩንም ለመቅረፍ በጊዚያዊነትና በዘለቄታዊነት ይረዳሉ የተባሉ የመፍትሄ ሀሳቦችም ቀርበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት በቻይና የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ችግሩን በጊዚያዊነት ለመቅረፍ ከቻይና ጉሙሩክ አስተዳደር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች እንደሚደረጉ ያሳወቁ ሲሆን አገሪቱ ህጉን ያወጣችው ለሁሉም አገራት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ላኪዎች ያንን የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

የቻይና ገበያ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ባለሀብቶች ይሄንን የገበያ እድል በስፋት ሊጠቀሙ እንደሚገባም መጠቆማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛ ምስራቅ፣ ኤዥያ እና ፓስፊክ አገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ (ዶ/ር) የተፈጠረው ችግር አገርን ጥቅም ከማሳጣቱ ባሻገር በቻይና ገበያ ላይ ያለን ምቹ የገበያ ሁኔታ ኢትዮጵያ በአግባቡ እንዳትጠቀም የሚያደርግ በመሆኑ ባለድርሻ አካላትን ሁሉ ባካተተ መልኩ የመፍትሄ ሥራዎች መሰራት አለባቸው ብለዋል።