ወጣቶች ለሰላም ግንባታ ጉልህ ሚና አላቸው- ሙፈሪያት ካሚል

ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) –  የአፍሪካ ወጣቶች እምቅ አቅማቸውን በሳይንሳዊ መንገድ ከተጠቀሙ ለቀጠናው ሰላም ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

የምሥራቅ አፍሪካ የተጠባባቂ ኃይል የወጣቶች ሥልጠና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ይገኛል።

የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል የወጣትነት ዘመን ሁሉንም የመሞከር ፍላጎትና ጥረት የሚስተዋልበት መሆኑን ጠቅሰው በተሻለ አስተሳሰብ ታንጾ ራስን፣ ቤተሰብንና አገርን በሚጠቅም ጉዳይ ላይ ጎልቶ ከታየ አዎንታዊ ምላሽ ይኖረዋል ብለዋል።

አፍሪካ የቴክኖሎጂ ወይንም የፋይናንስ ሃብታም ሳትሆን የሰው በተለይም የወጣቶች ሃብታም ነች ያሉት ሚኒስትሯ ወጣቶች አስተሳሰባቸውንና እውቀታቸውን በማዳበር አገራቸውን ኃያላን አገራት የደረሱበት ደረጃ ማድረስ ይችላሉ ብለዋል።

ለዚህም እሴቶቻቸውንና ባህላቸውን ሳይለቁ ቀጠናው ሰላማዊና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴውም የተሻለ እንዲሆን አብሮነታቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቶች ሰላምን በመጠበቅ በመንከባከብ ብቻ ሳይሆን ሰላምን በማምጣት ፈር-ቀዳጅ መሆን እንዳለባቸው ማሳባቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

ሥልጠናው ሰላምን የሚሰብኩና በሰላም ዙሪያ መፍትሔን የሚያመጡ የአባል አገራት ልምዶችን የሚለዋወጡበት እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ሥልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በነገው እለትም በእንጦጦ ፓርክ የአረንጓዴ አሻራቸውን የሚያኖሩ ይሆናል።