ዋልታ ለአብርኆት ቤተ መጽሐፍ 3ሺሕ 150 መጻሕፍትን አበረከተ

ግንቦት 27/2014 (ዋልታ) ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ለአብርኆት ቤተ መጽሐፍ 3ሺሕ 150 መጻሕፍትን አበረከተ።

የኮርፖሬቱ ሥራ አስፈፃሚ ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር) ለማሰብ እና ለመመራመር የግድ ማንበብ በማስፈለጉ አሳቢያንን ለመፍጠር መጻሕፍትን መለገስ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ለአብርሆት ያበረከታቸው መጻሕፍት ፍልስፍና፣ ፖለቲካል ሳይንስ፣ ኢኮኖሚ፣ ባህልና  ጋዜጠኝነት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ውጭ ሊገኙ የማይችሉ ከ800 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ጥራዞች ለአብርኆት ተለግሰዋል።

ጥራዞቹ ዘ-ኢኮኖሚስት፣ ኒውስ ዊክ እና ዘ-ታይምስ መጽሔቶችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ሲታተሙ የነበሩ መጽሔቶችና ጋዜጦች ያካተቱ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ለአብርኆት ቤተ-መጽሐፍ የሚደረገው የመጻሕፍት ልገሳ እንዲጨምር ብሎም በየክልሉ ተመሳሳይ አብርኆቶች እንዲገነቡ ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት የድርሻውን እንደሚወጣ ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በዕለቱ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና ሜጋ መጽሐፍ አሳታሚ ድርጅት ለአብርኆት የመጻሕፍት ልገሳ አድርገዋል።

በምንይሉ ደስይበለው