ዋልታ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሥራ ትብብር ውል አደረገ

ጥቅምት 17/2014 (ዋልታ) – ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ከ11 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን ውል ተፈራርሞ ወደ ሥራ መግባቱን አስታወቀ፡፡
የኮርፖሬቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ንጉሤ መሸሻ (ዶ/ር) እንደገለጹት ስምምነቱ ዩኒቨርሲቲዎቹ የያዙትን ራዕይ፣ ተልዕኮና አፈጻጸም መነሻ በማድረግ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀት፣ በመተንተን እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በቴሌቪዥን ቻናሎች ማሰራጨትን ይመለከታል፡፡
ዋልታም እነዚህን የድምጽና የምስል መረጃዎች በቴሌቪዥን ቻናሉ፣ በሬዲዮ ጣቢያው፣ ኮርፖሬቱ በሚያስተዳድራቸው የተለያዩ የማህበራዊ የትስስር ገጾች፣ ዌብ ሳይትና ዩቲዩብ ቻናሉ ላይ በማሰራጨት ለላቀ ጥቅም እንዲውሉ ለማስቻል የተደረሰ ስትራቴጂክ አጋርነት መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
እንደ ንጉሤ (ዶ/ር) ገለጻ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁልፍ ተልእኮዎች ዋነኛ ተግባራት የሆኑትን የጥናትና ምርምር እንዲሁም ማህበረሰብ አቀፍ የልማት ተግባራት ላይ በማተኮር ተከታታይነት ያለው የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራዎችን ይሰራሉ፡፡
ኮርፖሬቱ የትብብር ሥራውን በብቃትና በጥራት የሚያስተባብሩ እና የሚፈፅሙ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን በመመደብ እንደሚያከናውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡
ዋልታ የሳይንስ፣ የፈጠራና የምርምር ቴሌቪዥን ቻናል ለመጀመር እቅድ እንዳለው ያነሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተለይ በምርምሩ መስክ በርካታ ስራዎች በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
እነዚህ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራዎች በየዩኒቨርሲቲዎቹ የልህቀት ማዕከላት የሚሰሩ ስራዎችን የማስተዋወቅ፣ የስራዎቹ ጽንሰ-ሃሳብ እንዲሰፋ የማስቻልና የልምድ ልውውጥ እንዲፈጠር የማድረግ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
ስምምነቱን ካደረጉት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲውን የሚያስተዋውቅ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ስራዎችን ከዋልታ ጋር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት አመልክተዋል።
ሁለቱ ተቋማት 10 ዓመታት የዘለቀ የስራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት በመመስረት ጥራትን በማስተዋወቅ ረገድ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አህመድ ከሊል (ዶ/ር) የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት የሚቀይሩ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለመስራት እንዲሁም የባሌ አካባቢ የሚገኙ የቱሪዝም ሃብቶችን ለማስተዋወቅ ከዋልታ ጋር የተደረገው ስምምነት ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ተናግረዋል፡፡
የመደዋላቡ ዩኒቨርሲቲ መለያው የሆነውን ዘርፍ በማጥናት ለብዝሃ ህይወትና ቱሪዝም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ የሶፎመር ዋሻ፣ የባሌ ተራራ፣ ድሬ ሸክ ሁሴን በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚገኙ የቱሪዝም ሐብቶች ናቸው፡፡
የጂማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዋልታ ወደ ህብረተሰቡ ተደራሽ ከሚሆንባቸው ፕሮግራሞቹ በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የምርምር ሥራዎችን በጋራ መስራት መቻሉ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል፡፡
ችግር ፈቺ እና ማህበረሰብ አቀፍ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርሱ ከዋልታ ጋር መስራት በመቻላችን ይህን ተግባር አጠናክረን ለመቀጠል ያስችለናል ያሉት ደግሞ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የመግባቢያ ሠነዱን መፈራረሙ የስትራቴጂክ አጋርነት በመመስረት የዩኒቨርሲቲውን ራዕይ፣ ተልዕኮና አፈጻጸም መነሻ በማድረግ የምስልና የድምጽ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን በአሁኑ የዋልታ ቴሌቪዥን ቻናል ላይ በማሰራጨት በላቀ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዲውል በትብብር መሥራት የሚያስችል ስምምነት በመፈጠሩ በምርምር ዘርፍ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ከዋልታ ጋር መስራት በመቻላቸውም ደስተኛ መሆናቸውን የዩኒርሲቲዎቹ ፕሬዝዳንቶች ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ከኮርፖሬቱ ጋር በትብብር ለመስራት ውል የገቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ አርባምንጭ፣ አዳማ፣ ወለጋ፣ መዳ ወላቡ፣ ጂንካ፣ አርሲ፣ ቦንጋ እና ሐራምቤ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
(በነስረዲን ኑሩ)