ዋና ዋና ከተሞችን በማዘመን የህዝብን የልማት ጥያቄዎች መመለስ ይገባል ተባለ

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) የክልሉን ዋና ዋና ከተሞች በማዘመን የህዝብ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ አለብን ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አዲሱ አረጋ ገለፁ።

የ”ስማርት አዳማ” ፕሮጀክት ፅንሰ ሃሳብ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት አስተባባሪው በክልሉ ከተሞች ያሉትን ዘርፈ ብዙ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ብልሹ አሰራሮችና ሌብነትን ለማስወገድ የአገልግሎት አሰጣጣችንን ወደ ዲጂታላይዜሽን መቀየር አለብን ብለዋል።

“ህዝቡ ከአመራሩ የሚጠብቀው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ነው” ያሉት አቶ አዲሱ፤ “ይሄን ማድረግ የምንችለው አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ዲጂታላይዝ ማድረግ ስንችል ነው” ብለዋል ።

በአዳማ በተለይ በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የመዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ ገቢዎችና የንግድ ተቋማትን ወደ ዲጂታላይዜሽን በማስገባት ረገድ ያሉ ጅምሮችን እንደ አብነት ያነሱት አስተባባሪው፤ እነዚህ ጥረቶች የሚበረታቱና በሌሎችም ከተሞች ተጠናክረው መቀጠል የሚገባቸው ናቸው ብለዋል።

የከተማዋን አገልግሎት ወደ ዲጂታላይዜሽን መቀየር ያስፈለገው “ህዝቡ እየጠየቀ ያለውን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ነው” ያሉት ደግሞ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ ናቸው።

በተለይም የህዝቡን ቅሬታ ለመፍታት አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው መሆኑንም አክለዋል።

ወንጀልና ህገ ወጥ አሰራርን ለመከላከልም የከተማዋን 18 ቀበሌዎች መሰረት ያደረገ “አዳማ ፖርታል የመረጃ መቀበያ ሲስተም” መዘርጋቱንም ከንቲባው አክለዋል።

እስከ ቀበሌ ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዲጂታል የመታወቂያ ካርድ እየተሰጠ ሲሆን ለማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችም የተሻሻለ አዲስ ሶፍትዌር በማበልፀግ ወደ ስራ መገባቱን ከንቲባው ገልጸዋል።

በመድrኩ የክልሉና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የአዳማ ከተማ ክፍተኛ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

አሳንቲ ሐሰን (ከአዳማ)