“ዐርበኝነት ማለት በሀገር ጉዳይ ላይ ለእውነት እና ለእምነት የሚከፈል መሥዋዕትነት ነው” – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ሚያዝያ 27/2014 (ዋልታ) “ዐርበኝነት ማለት በሀገር ጉዳይ ላይ ለእውነት እና ለእምነት የሚከፈል መሥዋዕትነት ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 81ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓልን በማስመልከት  በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፣ “ጀግኖች እናቶቻችን እና አባቶቻችን የሀገራቸውን ነጻነት እና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሲሉ ምትክ የሌለውን ሕይወታቸውን ከፍለዋል።” ብለዋል።

ዛሬ ይሄንን የሕይወት ዋጋ የከፈሉትን ዐርበኞቻችንን በክብር እናስባቸዋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “እኛም ልጆቻቸው፣ ቀደምት ዐርበኞች ላከበሯት ሀገራችን ልዕልና እና ብልጽግና ለማጎናጸፍ ዋጋ የምንከፍል ተተኪ ዐርበኞች መሆናችንን ልናረጋግጥ ይገባናል።” ሲሉም አሳስበዋል።