“ዓለም ስለኢትዮጵያ ያለው አረዳድ ትርክቱ ሊቀየር ይገባል” – ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) አሁን ላይ በሀገሪቱ የሚሰሩት የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ዓለም እየተረዳበት ያለው ሁኔታ ትርክቱ ሊቀየር እንደሚገባ የሚያመላክት ነው ሲሉ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በባሌ ዞን፣ ሲናና ወረዳ 42 ሺሕ 901 ሔክታር መሬት ላይ በክላስተር እየለማ ያለን የስንዴ ማሳ ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ተሳታፊ የነበሩት ኦባሳንጆ በሰጡት አስተያየት “አሁን በሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ እየተሰራ ያለው ልማት ኢትዮጵያ ለሕዝቧ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ጭምር ለውጥ ማምጣት የምትችል ሀገር መሆኗን የሚያሳይ ነው” ሲሉ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ያጋጠመውን ጦርነት ብቻ ሳይሆን እየተሰሩ ያሉ አበረታች የግብርና እንቅስቃሴዎችን መመልከት ችያለሁ ያሉት ልዩ መልዕክተኛው መሬት ላይ ያለውን ይህን እውነት ዓለም እንዲገነዘብ በተደጋጋሚ ማስረዳት እና ማሳየት እንደሚገባ ገልፀዋል።
ዓለም ስለጦርነቱ መዘገብ ብቻ ሳይሆን ለሰላም ዋስትና የሚሆኑ የተሰሩ የልማት ሥራዎችን ጭምር በመመልከት ኢትዮጵያን በዚህ ደረጃ ሊረዳት ይገባልም ብለዋል የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ ኡስማን ዲዮን በበኩላቸው በአፍሪካ በተለያዩ ቦታዎች የተሰሩ የግብርና ልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን አንስተው በኢትዮጵያ የተሰራው የግብርና ልማት ትልቅ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢብኮ ነው የዘገበው።
ኢትዮጵያ የያዘቸውን መሰል የልማት እንቅስቃሴ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና ስለሚኖረው የዓለም ባንክ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ኃላፊው።