ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት የሚፈጽማቸውን የሽብር ድርጊቶች በጽኑ ሊያወግዝ ይገባል

ነሀሴ 14/2013 (ዋልታ) – ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአሸባሪው ሕወሓት የሚፈጽማቸውን የሽብር ድርጊቶች በጽኑ ሊያወግዝ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት የውጭ ቋንቋዎች እና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ አሸባሪው ሕወሓት አሁንም የሽብር ድርጊቱን ቀጥሏል።

በተለይም በቅርቡ በአማራ ክልል የሽብር ጥቃት እየፈጸመ ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ ሠላማዊ ሕዝቡን እያሸበረ መሆኑን ተናግረዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን አሸባሪው ቡድን የግለሰቦችን ንብረት በመዝረፍ፣ ሆስፒታልን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረ ልማት አውታሮችን እያወደመ እኩይ ተግባሩን እንደቀጠለበት ተናግረዋል።

ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች “የመከላከያ ሠራዊት የሚገኝበትን ሥፍራ ጠቁሙ” በማለት ንጹሃንን እያንገላታ፣ እያገተና እየገደለ መሆኑንንም ነው ያብራሩት።

በቅርቡም በደብረ ታቦር ከተማ ቡድኑ ባስወነጨፈው ከባድ መሳሪያ ንጹሃን ዜጎች ሰለባ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህም አሸባሪ ቡድኑ “አፍራሽ ዓላማ ያነገበ መሆኑን አመላካች ነው” ብለዋል።

ጎን ለጎንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የአሸባሪ ቡድኑ የፕሮፓጋንዳ ክንፍ የሐሰት መረጃ እንደሚያሰራጭ ጠቁመው፤ የፕሮፓጋንዳ ክንፉ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችን ስም የማጥፋት ዘመቻ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

በተጓዳኝም ከቡድኑ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች በአዲስ አበባና በክልሎች የኢኮኖሚ አሻጥር ለመሥራት ሲቀናጁ እንደተደረሰባቸው መረጃ ጠቅሰው አስረድተዋል።

ይህ አሸባሪ ቡድን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት አስጊ መሆኑን በአጽንኦት የገለጹት ሃላፊዋ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቡድኑን ሊከታተለውና የሚሰራውን ሥራም በጽኑ ሊያወግዘው እንደሚገባ አሳስበዋል።

አሸባሪው ሕወሃት ከአፋርና ከአማራ ክልል የተፈናቀሉ ከ300 ሺ በላይ ዜጎች ከመንግሥት ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በመሆን ሰብዓዊ እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ክልል የሚገባውን የሰብዓዊ እርዳታና በአሸባሪው ቡድን ለተፈናቀሉ ዜጎች  አስቸኳይ ድጋፍ ለመስጠት የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በቱርክ ያደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ስኬታማና የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ መሆኑን አብራርተዋል።

ጉብኝቱ ሁለቱ አገራት ግንኙነት የመሰረቱበትን 125ኛ ዓመት በሚያከብሩበት ወቅት መሆኑን የጉብኝቱን ታሪካዊ ፋይዳ እጅግ የጎላ ያደርገዋል ሲሉ ነው የተናገሩት።

መሪዎቹ በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸው፤ በተለይም ፕሬዚዳንት ጣይፕ ኤርዶጋን ለኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አብራርተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ይበልጥ ሊያጠናክሩ በሚችሉ በተለያዩ ዘርፎች አራት ዋና ዋና ሥምምነቶች መፈራረማቸውን ነው ኃላፊዋ የገለጹት።

ሥምምነቶቹም በዋናነት በውኃ፣ በወታደራዊና በፋይናንስ ድጋፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።