ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ታሊባንን ለመዋጋት አንድ መሆን ይገባል – ተመድ

ነሐሴ 11/2013 (ዋልታ) – የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በአፍጋኒስታን የሚታየውን የሽብር እንቅስቃሴ ለማውገዝ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በህብረት መስራት እንደሚገባው  አሳሰቡ፡፡

በሽብር ቡድኑ ታሊባን የምትታመሰውን አፍጋኒስታ እንደገና ለአሸባሪ ድርጅቶች መጠቀሚያ እንዳትሆን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንድ መሆን አለበት ብለዋል።

የአፍጋኒስታኑ ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ ወደ ውጭ ከሸሹ በኋላ  የታሊባን ታጣቂዎች ወደ ዋና ከተማው ካቡል መግባታቸውን ተከትሎ በኒው ዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ዋና መሥሪያ ቤት ስብሰባ ተደርጓል።

በስብሰባቸውም አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለፀጥታው ምክር ቤት እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋራ እንዲቆሙ እና በትብብር እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አክለውም ሀገራት በአፍጋኒስታን የሚንቀሳቀሰውን ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን ለማጥፋት እና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ በሚችሉት አግባብ ሁሉ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

የታሊባን ተዋጊዎች ካቡልን በመቆጣጠራቸው ምክንያት አፍጋኒስታኖች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሙሉ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

ዋና ፀሃፊው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአፍጋኒስታን ምድር የሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር በአንድ ድምጽ እንዲናገር ማሳሰባቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

ጉተሬዝ አክለውም ታሊባን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕጎችን፣ የሰዎችን መብቶች እና ነፃነቶች እንዲያከብርና እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።