ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት እየፈፀመ ያለውን የሽብር ስራ ሊያወግዝ እንደሚገባ ተገለጸ

ጥቅምት 25/2014 (ዋልታ) ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ከተዛቡ መረጃዎች በመውጣት የሕወሓት የጥፋት ቡድን እየፈፀመ ያለውን የሽብር ስራ ሊያወግዝ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

አምባሳደር ሬድዋን በኢትዮጵያ ከዴንማርክ አምባሳደር ኪራ ስሚዝ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት እና  በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ላጋጠማት ችግር ዋና ተጠያቂው የሕወሓት ቡድን መሆኑን አብራርተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በተዛቡ መረጃዎች ላይ ተመስርተው በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያልተገባ ጫና እየፈጠሩ ያሉ አካላት እውነታውን በመረዳት አካሔዳቸውን ቆም ብለው መፈተሽ አለባቸው ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ኪራ ስሚዝ በበኩላቸው ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ጊዜ የዘለቀ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላት መሆኑን አንስተው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ እያደረገች መሆኗንም ጠቅሰዋል።

አምባሳደሯ አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ቀውስ በርካታ ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው ለማድረግ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን አለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሓትን የሀሰት መረጃ ከመስማት ታቅቦ መሬት ላይ ያለውን እውነታ መመርመር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር ለመፍታት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗንም ለአምባሳደሯ ማብራራታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡