ዓመታዊው የአገው ፈረሰኞች በዓል ጥር 23 እንደሚከበር ተገለፀ

ጥር14/2014 (ዋልታ) የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ጥር 23 ለ82ኛ ጊዜ ዓመታዊው በዓል ለማክበር አስፈለጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ፡፡
በዓሉ ዓድዋ ላይ የሀገርን ነፃነት ለማስከበር የተዋደቁትን የሀገር ባለውለታዎችን በማሰብ እንደሚዘከር የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ሰብሳቢ ጥላየ አየነው ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ 59 ሺሕ 323 አባላት እንዳሉት የተነገረ ሲሆን በዓድዋ ጦርነት ጀግኖችን በማገልገል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱትን ፈረሶች ከዓድዋ ድል በኋላ ልክ እንደ ጀግኖች አርበኞች ውለታቸውን በማሰብ ማኅበሩ በ1932 ዓ.ም እንደተመሰረተ ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩ ሀገር በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የተጋረጠባትን ፈተና ለመመከት ከ1 ሺሕ 300 በላይ የፈረሰኛ አባላትን ለኅልውና ጦርነት ማሰለፉንና ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የማኅበሩ ሰብሳቢ አስታውቀዋል፡፡
ማኅበሩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ከእንጅባራ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኘውን የዘንገና ሀይቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ሥራ መጀመሩን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ጥር 23 የሚከበረው ዓመታዊ የአገው ፈረሰኞች በዓል ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አርቲስቶች፣ ዲያስፖራዎች እና መታደም የሚፈልጉ ሁሉ እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡