ዕድሮች የአብሮነት፣ የአንድነትና የመተባባር ቅንጅት ማሳያ ናቸው – ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ግንቦት 06/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ የሚገኙ ዕድሮች የአብሮነት፣ የአንድነት እና የመተባባር ቅንጅት ማሳያ በመሆናቸው የሚደርጉትን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ይበልጥ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
“እድሮች ለሀገር ሠላም እና ብልጽግና ” በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባ ከተማ ዕድሮች ዓመታዊ ጉባዔ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል፡፡
በዓመታዊ ጉባዔ ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባዋ ዕድሮች ዘር፣ሃይማኖት፣ቋንቋ እና ብሄር ሳይለዩ ከጥንት ጀምሮ የአንዱን ሀዘን በመካፈል በማህበራዊ ህይወት የሚገጥሙንን ሸክም በማቃለል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል፡፡
በአካባቢ ጽዳትና ሰላም፤ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሎም ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ከነበሩ ተቋማት አንዱ የዕድሮች ስብስብ መሆኑንም ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡
የምንከበረው፤ የምንጠነክረው እና የምንፈራው አንድ ስንሆን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ የሀገራችንን ብልጽግና ለማስቀጠል በሚደረገው ርብርብ ዕድሮች የበኩላቸውን ድርሻ በማበርከት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተፈራ ሞላ በበኩላቸው በከተማዋ የሚገኙ ከ7 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑ ዕድሮች በከተማዋ የልማት እና የሰላም ተሳትፎ ላይ ግንባር ቀደም በመሆን ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሆነ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬተሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡