አገር እንድታድግ እና ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲሰፍን ምሁራን ከዝምታ ወደ ይመለከተኛል ስሜት ሊሸጋገሩ ይገባል ተባለ።
“ብሄራዊ ጥቅሟ እና ደህንነቷ የተረጋገጠ አገር በመገንባቱ ሂደት የምሁራን ሚና” በሚል የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩን የሰላም ሚኒስቴር እና ኮተቤ ሜትሮፖሊያን ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያዘጋጀ ሺኆን፣ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷ የተከበረ እና ብሄራዊ ጥቅሟ የተረጋገጠ አገር እንድትሆን ምን ማድረግ አለብን፣ ከሁሉ በላይ የምሁራኑ ሚና ምን መሆን አለበት? በሚል ውይይት ተደርጓል።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት በዘመናት ልዩነት ፀንታ የኖረች በመሆኗ ሊያፈርሷት ቢሹ የማትፈርስ፣ ሊጥሏት ቢመኙም የማትወድቅ አገር ናት ያሉ ሲሆን፣ ሀገሪቷን ወደ ከፍታው ማማ ለማድረስ የምሁራኑ ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የህግ እና ታሪክ መምህር የሆኑት ዶ/ር አልማው ክፍሌ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ህግ እና ሌሎች ዘርፎች ያሉ ምሁራን ተሳታፊ ባለመሆን እጃቸውን አጣጥፈው ተመልካች በመሆናቸው አገሪቷ በታሪክ፣ ፓለቲካም ይሁን በኢኮኖሚው ዘርፍ ወደ ኋላ እንድትቀርና ዋጋ እንድትከፍል ሆኗል ብለዋል።
በመድረኩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፣ በሀገር በቀል እውቀቶች እና ልምዶች ውስጣዊ ችግሮቻችንን ከመፍታት አንፃር የባህል ተቋማት ሚና እንዲሁም ህዳሴ ግድብ አንድነታችንን እና ሉአላዊነታችንን ከማስጠበቅ አንፃር የዜጎች የአርበኝነት ተሳትፎ አስፈላጊነት በሚል ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
(በቁምነገር አህመድ)