ዘመቻው በሚጠይቀው ልክ ሃብት ለመሰብሰብ ጥሪ

መስከረም 11/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ የጎላ ቢሆንም የኅልውና ዘመቻው በሚጠይቀው ልክ እና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚያስችል ሃብት እየተሰበሰበ ባለመሆኑ ኢትዮጵያዊያን የበለጠ እንዲተባበሩ ተጠየቀ፡፡

የአማራ ክልል ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ለኅልውና ዘመቻው እየተካሄደ ባለው ድጋፍ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

በዚህም የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ሁሉም ዜጋ በጦር ግንባር መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የጸጥታ ኃይሎችና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሃብት አሰባሰብ የመንግሥት ሰራተኞች ጥሩ አፈፃፀም ቢኖራቸውም ከነጋዴው፣ ከገጠር እና ከከተማ ነዋሪዎች የተሰበሰበው ጥሬ ገንዘብ የኅልውና ዘመቻው በሚጠይቀው መጠን አይደለም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ወረራ ባልተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የሽብርተኛው ሕወሓት ወራሪ ቡድን የፈፀመውን ውድመት ሊያካክስ የሚችል ሃብት በመስጠት የወገን አለኝታነቱን ማሳየት እንደሚገባ መናገራቸውን ከአሚኮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡