ዛሬ ኢትዮጵያውያን ለነገው ትውልድ የሚተርፍ ታላቅ ስራን የሚሰሩበትና ለሀገራቸውም ስጦታን የሚያበረክቱበት ዕለት ነው -ሰላማዊት ካሳ


ነሀሴ 17/2016 (አዲስ ዋልታ) ዛሬ ኢትዮጵያውያን ለነገው ትውልድ የሚተርፍ ታላቅ ስራን የሚሰሩበትና ለሀገራቸውም ስጦታን የሚያበረክቱበት ዕለት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በዛሬው እለት መላው ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀንበር ከ600 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለትውልድ የሚተርፍ ገጸ በረከት የሚሰጡበት ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል፡፡

ህዝቡ በጂኦሪፈረንስድ በተለዩ ቦታዎች ችግኝ ለመትከል እየተመመ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ችግኝ ተከላው መጀመሩንም ይፋ አድርገዋል።

ቀኑን ሙሉ በሚከናወነውና “የምትተክል ሀገር፤ የሚያጸና ትውልድ“ በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ መርሃግብር ለነገዋ ኢትዮጵያ አሻራችንን የምናኖርበት ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ባለፉት ዓመታት የደን ሽፋንን ለመመለስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከተረጂነት የመላቀቅ ሂደትን ለማገዝ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል።