ዜጎች በአካባቢያቸው ያለውን ጸጋ ተጠቅመው በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ትኩረት ተሰጥቷል – ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ሚያዝያ 25/2016 (አዲስ ዋልታ) ዜጎች በአካባቢያቸው ያለውን ጸጋ ተጠቅመው በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በባህርዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 18 ሺሕ ዜጎች ማዕድ የማጋራት ስራ ተከናውኗል።

በማዕድ ማጋራት መርኃግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ለድሃ ተኮር የልማት ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

በዚህም ዜጎች የአካባቢያቸውን ጸጋ ተጠቅመው በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዜጎችን ወደ ሥራ ለማሰማራት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን አቅመ ደካሞችንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝና መደገፍ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የማዕድ ማጋራት ተግባር ላይ ለተሳተፉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡንና አጋር አካላትን በማስተባበር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማገዝ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዛሬ የተከናወነው ማዕድ ማጋራት ከተማዋ ወደ ቀደመ ሰላሟ መመለሷን ያሳያል ብለዋል።

ማዕድ የማጋራት ተግባሩ ከአጋር አካላት፣ ከህብረተሰቡና ከክልል የተለያዩ ቢሮዎች በተሰበሰበ ገንዘብ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምርያ ኃላፊ ሰብለ ዘውዱ ናቸው።

በዚህም 9 ሚሊዮን 832 ሺሕ 441 ብር የሚገመት የማዕድ ማጋራት ተግባር መከናወኑን ገልጸው ማዕድ ማጋራቱም ለ18 ሺሕ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ተጠቃሚ ማድርጉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡