ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች እጅግ አስፈላጊ ናቸው – የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን

ግንቦት 5/2016 (አዲስ ዋልታ) በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ዜጎች በአንጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ በንቃት የመሳተፋቸው አስፈላጊነትን በተመለከተ ባወጣው ማብራሪያ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም ብሏል፡፡

ዜጎች እና ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ በንቃት መሳተፋቸው አስፈላጊነትና የሚያስገኛቸውን ውጤቶችንም በተመለከተ እንዲሁ፡፡

በዚህም አካታች የሆነ ውሳኔ ሰጪነትን ለማረጋገጥ እንደሚጠቅም ገልጾ በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ ከዜጎች የሚሰበሰቡ አጀንዳዎች ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ያስችላል ነወ ያለው፡፡

በሂደቱም ሁላችንም ሀሳባችንን ለማቅረብ በንቃት መሳተፋችን ሂደቱን ስኬታማ ከማድረጉም በላይ በሀገራችን ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለመጫወት በር ይከፍትልናል ብሏል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በዜጎች እና ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡ የአጀንዳ ሀሳቦች ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸውን ስሜት እና ፍላጎት እንዲያንፀባርቁ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለተፈጠሩ ችግሮች የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ መንገድ ከፋች ነው ሲልም ገልጿል፡፡

የሀገራዊ ምክክር በተለያዩ አጋጣሚዎች በሀገራችን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር ውስጥ ድምፃቸው ጎልቶ ያልተሰማ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሀሳቦችን ለማስተጋባት መደላድል ይፈጥራል ብሏል፡፡

እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸው ሀሳባቸውን ማቅረባቸው በሀገራችን የዲሞክራሲ ልምምድ ላይ በጎ ተፅዕኖ ይኖረዋል ሲልም አክሏል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ሂደት ባለቤት ህዝብ እንደመሆኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ዜጎች ሀሳቦቻቸውን በቀጥታም ይሁን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሲያቀርቡ በሂደቱ ሊኖራቸው የሚገባው የባለቤትነት መብት እንዲረጋገጥ መንገዱን ይጠርግላቸዋል ብሏል ኮሚሽኑ፡፡

ከዚህ ባሻገር በሚቀርቡ የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ዜጎች የጉዳዩ ማዕከል ሆነው በሀገራዊ ምክክሩ ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በጋራ ማመንጨት ይችላሉ ብሏል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በእውነት እና በግልፅ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን ማቅረባቸው የጋራ መተማመንን ለመገንባት ዕድል ይፈጥርላቸዋል ሲልም ገልጿል፡፡

በሂደቱም ሀሉም አካላት ካለፈው ተምረው ስለ ነገዋ የጋራ ሀገራቸው መክረው የማህበራዊ ውሎቻቸውን ያድሳሉ ብሏል ኮሚሽኑ በማብራሪያው፡፡

በመሆኑም በመላው ዓለም ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራችን መፃኢ ተስፋ ላይ ጉልህ ሚና በሚኖረው በዚህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ተሳታፊ በመሆን ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በጋራ ማምጣት እንድንችል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪውን በታላቅ አክብሮት ያቀርባልም ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ በመደበኛ መልክ አጀንዳዎችን የሚሰበስብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እርስዎ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ቢነሳልኝ የሚሉትን አጀንዳዎች በቡድን ወይም በግል በፖስታ ሳጥን ቁጥር፡ 32623 አዲስ አበባ
በኢሜል፡ ethiopianndc@gmail.com በኮሚሽኑ ድረ-ገፅ፡ https://ethiondc.org.et በመጠቀም ማቅረብ እንደሚችሉም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡