የ11ኛው ክልል ምስረታ የበርካታ ዓመታት የህዝብ ጥያቄ ምላሽ መሆኑን የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ገለጸ

ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

ኅዳር 13/2014 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምስረታ የበርካታ ዓመታት የህዝብ ጥያቄ ምላሽ መሆኑን የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ

የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢው ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በስሩ አምስት ዞኖችን እና አንድ ልዩ ወረዳ የያዘው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አንድ የሆነ ማህበረሰብ፣ ተመሳሳይ ስነ ልቦና እንዲሁም በታሪክ እና በባህል ተያያዥ የሆኑ ህዝቦችን የያዘ ክልል መሆኑን ገልፀዋል።

ለበርካታ ዓመታት የህዝብ ጥያቄ ሆኖ የቆየው የአደረጃጀት ጥያቄ በህዝበ ውሳኔ ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት በማድረግና የህዝብ አስተያየትን በመቀበል ለክልል ምስረታው በቂ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ 11ኛው ክልል ሆኖ ነገ የሚመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በርከት ያሉ አዳዲስ የአሰራር ሂደቶች፣ የስልጣን ክፍፍል እንዲሁም ከአንድ በላይ ርዕሰ ከተሞች ይኖራሉ ተብሏል።

የክልሉ ባንዲራ፣ የዕዳ አከፋፈል እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በተቋቋሙት ኮሚቴዎች ስር በጊዜ መፍትሄ እንደሚኖረው ተገልጿል።

ከነባሩ ክልል ስልጣን ተቀብለናል ያሉት የኮሚቴ ሰብሳቢው በነገው እለት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ ይመሰረታል ብለዋል።

በቁምነገር አሕመድ (ከቦንጋ)