የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ጥቅምት 02/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የምርጫ ውጤትን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሀረሪ ክልልን ጨምሮ መስከረም 20 ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በማስመልከት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውጤት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የእንኳን ደስ አለን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አለን መልዕክት እንዳሉት፣ የሀገራችን ሕዝብ ዝናብና ፀሐይ ሳይበግረው፣ በረጃጅም ሰልፎች ሳይሰላች የሚፈልገውን ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ካለምንም ተፅዕኖ መርጧል።

“እንደ እኛ እምነትም በዚህ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ሕዝባችን ነው”።

ከሕዝባችን በመቀጠል በዲሞክራሲና በሕዝብ ድምፅ ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት ፣ ሀሳብና ፖሊሲያቸውን ለሕዝብ አቅርበው ብርቱ ውድድር ያደረጉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ድል አድራጊዎች ናቸው ብለዋል።

በክልሉ መስከረም 20 የተካሄደው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በተለይም ምርጫ ቦርድ ያለ ምንም ተጽእኖ የምርጫውን ሂደት በገለልተኛ የዳኘበት ምርጫ መሆኑ ልዩና ታሪካዊ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የምርጫ ቦርድ ዳኝነት እንዲሳካ ደግሞ ቁጥራቸው የበዙ የግልና የመንግሥት ሚዲያዎች ፣ የሲቪክ ተቋማት ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎችም ተቋማት በግልጽ የተከታተሉት መሆኑ ሂደቱን ከመቼም ጊዜ በላይ ተአማኒነቱና ዲሞክራሲያዊነቱ የተጠበቀ እንዲሆን አስችሏልም ብለዋል።

በምርጫው አሸናፊና ተሸናፊን ሳይሆን ጠያቂና ተጠያቂ ያለበት የዲሞክራሲ ሥርዓትን በመሆኑ ያሸነፉት በምርጫው የተሳተፉት ሁሉም አካላት ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህም የሀገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አንድ እርምጃ ያስኬደ በመሆኑ ፓርቲያቸው ብልፅግና ከምንም በላይ ቀዳሚ ድሉ አድርጎ እንደሚመለከተው ጠቁመዋል።

“ፓርቲያችን በሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ ሀገርን ለማስተዳደር መመረጡ ከአሸናፊነት ይልቅ ኃላፊነት ፣ ከድል አድራጊነት ይልቅ ታላቅ የሆነ ሀገራዊ አደራ እንዲያድርብን አድርጎናል”።

በክልሉ ብልፅግና ፓርቲ በህዝብ መመረጡ በዕቅድና በፖሊሲ የያዛቸው ግቦች እንዲያሳካ እና ዐቅሙን ሁሉ አሟጦ ለመሥራት ቆርጦ እንደተነሣ አበስራለሁ ሲሉም ተናግረዋል።

የተፎካካሪ ፓርቲዎች በቀጣይም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን መሬት እንዲረግጥ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ያመሰገኑት ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በተለይም የምርጫ ቦርድ አመራሮችና ሠራተኞች ፣ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ከግራ ከቀኝ የሚመጡትን ጫናዎችና በውጣ ውረዶች ሳይበገሩ ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።

ከሀረሪ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው  በተመሳሳይ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ጉልህ ሚና ለተጫወቱ የፌደራልና የክልል የጸጥታ አካላት ፣ ተገቢውን መረጃ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ወደ ሕዝቡ እንዲደርስ ላደረጉ የሚዲያ ተቋማትን አመስግነዋል።