የሀዋሳ ከተማ የመግቢያ በር ግንባታ ተጀመረ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የሲዳማን ሕዝብ ባህል የሚወክል እና ለሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ ውበት የሚሆን የከተማ መግቢያ በር ግንባታ ፕሮጀክት አስጀምሯል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጸጋዬ ቱኬ ወደ ሀዋሳ ከተማ የሚመጡ እንግዶች የሲዳማን ሕዝብ ባህል መገለጫዎች የማወቅ ዕድል የሚፈጥር በር ነው ብለዋል።

የመግቢያ በሩ ኢትዮጵያን በኪነ-ህንጻ ጥበብ በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ያደርጋታልም ተብሏል።

የመግቢያ በሩ የሲዳማ ሕዝብ መገለጫ የሆነው ሻፌታና ሌሎች ባህላዊ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ነው ያሉት።

ሀዋሳ ከተማን ከዓለም ዐቀፍ ከተሞች ተወዳዳሪ ለማድረግ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ነው ያሉት ከንቲባው አዲሱ የከተማዋ በር ሀዋሳን የማስዋብ ፕሮጀክት አንዱ አካል ነው ብለዋል።

የከተማ መግቢያ በሩ ዲጅታል ማስታወቂያ፣ የመብራት፣ የድምጽ እና የደኅንነት መቆጣጠሪያ ሲስተም የሚዘረጋለት መሆኑን ተናግረዋል።

የመግቢያ በሩ የ8 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ከዛ በላይ ከፍታ ያላቸው መኪናዎች ሲመጡ ማሳለፍ የሚችል ተለዋጭ መንገድም ይኖረዋል ተብሏል።

በሩ ጥቁር ውሃ ተብሎ በሚጠራው የሀዋሳ መግቢያ ነው የሚገነባው።

እንየው ቢሆነኝ (ከሀዋሳ)