የሂዩማን ራይት ዎች ዋና ዳይሬክተር ኃላፊነታቸውን በመጪው ነሐሴ ሊለቁ ነው

ሚያዝያ 18/2014 (ዋልታ) ሂዩማን ራይት ዎችን ለሦስት አስርተ ዓመታት አካባቢ በዋና ዳይሬክተርነት የመሩት አሜሪካዊ ኬኔዝ ሮዝ ኃላፊነታቸውን በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ እንደሚለቁ አስታወቁ፡፡

“ሂዩማን ራይት ዎችን ለሦስት አስርተ ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት በመቻሌ ታድያለው፤ ከሥራ ባልደረቦቼ እና ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን የሰው ልጆችን ሰብኣዊ መብት ለመጠበቅ የሚያስችል ዓለም ዐቀፍ ተፅእኖ ፈጣሪ ድርጅት ለመገንባት ችለናል፡፡ ነገር ግን የስልጣን በትሩን ለተተኪ የማስተላለፍበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ በመጪው ነሐሴ ሥራዬን አቆማለሁ፡፡” ይላል ኬኔዝ ሮዝ ኃላፈነታቸውን ስለመልቀቃቸው ይፋ ያደረጉበት የቲዊተር ጽሑፋቸው፡፡

ኬኔዝ ሮዝ ተቋሙን ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በዋና ዳይሬክተርነት የመሩ ሲሆን በስልጣን ዘመናቸው ተቋሙን ከአካባቢያዊ የመብት ጠበቂ ኮሚቴነት ወደ አንድ የተዋሃደ ዓለም ዐቀፍ ተቋም ማሳደግ መቻላቸውን ቢሯቸው ያወጣው መግለጫ ያትታል፡፡

የሰውዬው ሥራ የመልቀቅ ዜናን ተከትሎ እየተሰጡ ያሉ አስተያየቶች የተደበላለቁ ስሜቶችን በማስተናገድ ላይ ናቸው፡፡

በዚህም አንዳንዶች ኬኔዝ ሮዝ ለሰው ልጆች መብት መጠበቅ ሳይታክቱ የሰሩ ብለው ሲያወድሷቸው ሌሎች ደግሞ የምዕራባዊያን የመንግሥት የሥርዓት ለውጥ መሳሪያ አድርገው ይስሏቸዋል፡፡

አንዳንዶች ከኔዝ ሮዝ ዓም ዐቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማቋቋም ያደረጉትን አስተዋጽኦ ሲያወድሱ ሌሎች ደግሞ እሳቸው የሚመሩት ተቋም የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ሲካሄድ ያሳየውን ቸልተኝነት ይጠቅሳሉ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ ሂዩማን ራይተስ ዎች ባወጣቸው ሪፖርቶች ከፍተኛ ተቃውሞ ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡