የሃይማኖት አባቶች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

በሕዝቡ ውስጥ ፍቅር፣ አንድነት፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲሰርፅ የሃይማኖት አባቶች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎቸ ጋር ተወያይተዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶቹ ወደ መቀሌ ማቅናት በትግራይ ክልል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከርና በሕግ ማስከበሩ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ማጽናናትን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

የሃይማኖት አባቶቹና የአገር ሽማግሌዎቹ መቀሌ እንደደረሱ ከከተማዋ የአገር ሽማግሌዎችና የነዋሪ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም የሃይማኖት አባቶች ኢትዮጵያ ሠላም እንድትሆን፤ ስለ አገሪቷም መፀለይ እንደሚገባቸው ተገልጿል።

በውይይቱ የተገኙ ነዋሪዎች የሃይማኖት አባቶች ሠላም ለማስመለስና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን የማበረታታት ሃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

“ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን በመሆን መልካም ስራዎችን ማገዝ፣ ሕዝቡን ማገልገልና ስለ ሠላም መስበክ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል፡፡

ሕዝቡ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በመከባበርና በመተሳሰብ እንዲኖር የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍ ያለ እንደሆነም ነዋሪዎቹ አመለክተዋል፡፡

በሁሉም የእምነት ተቋማት ስነ-ልቦናን የሚያነቃቁ የተለያዩ መድረኮች መዘጋጀት እንዳለባቸውም ነው ነዋሪዎቹ የጠቆሙት፡፡

የሃይማኖት አባቶቹ በበኩላቸው ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ለወደፊትም ይህ ድርጊት እንዳይደገም ትውልድም ተስፋ እንዳይቆርጥ የማረጋጋት ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ወደ መቀሌ የመጡበት ዋናው ዓላማም ከሕዝቡ ጎን መሆናቸውን ለማረጋገጥና ሕዝቡን ለማጽናናት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለሕዝብ ፍቅርና ርህራሄ ማሳየት፣ ስሜቱ የተጎዳንም ስሜቱን መረዳትና ማጽናናት የሃይማኖት አባቶቹ በመቀሌ ቆይታቸው የሚተገብሩት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶቹና የአገር ሽማግሌዎቹ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና በመቀሌ ከሚገኙ የእምነት ተቋማት አባቶች ጋርም እንደሚወያዩ ኢዜአ ዘግቧል፡፡