የሀይቲ ፕሬዝዳንት በመኖሪያ ቤታቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት ተገደሉ

የሄይቲ ፕሬዝዳንት ጆቬለን ሞይስ

ሰኔ 30/2013 (ዋልታ) – የሀይቲ ፕሬዝዳንት ጆቬለን ሞይስ በመኖሪያ ቤታቸው ሳሉ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው ተነገረ።

የካሬቢያኗ አገር መሪ በመኖሪያ ቤታቸው መገደላቸውን ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ክላውድ ጆሴፍ አስታውቀዋል።

ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች በፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ፕሬዝዳንቱ መገደላቸውን እና ቀዳማዊ እመቤቷ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዝዳንቱ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት “ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር” በማለት የተቹት ሲሆን፣ የአገሪቱ ፖሊስ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጉዳዩን በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል ብለዋል።

የፕሬዝዳንቱ ግድያ የተሰማው የካሬቢያኗ አገር ሀይቲ ከመቼውም በላይ በፖለቲካ ልዩነት ሕዝቦቿ በተከፋፈሉበት ወቅት እና በኢኮኖሚ ድቀት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ተከስቶ በሚገኝበት ወቅት ነው ተብሏል።

የ53 ዓመቱ ጆቫኔል ሞይስ እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ ሀይቲን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ስልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት አስተዳደራቸው በብልሹ አሥራር እና ሙስና ሲወቀስ የቆየ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ ተቃውሞንም ሲያስተናግዱ ቆይተዋል ሲል ዘገባው አስታውሷል።