የህወሓት አመራሮች በስብሰባዎች ላይ ባለስልጣናትን ያሰልሉ ነበር- አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ

አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ

የህወሓት አመራሮች በስብሰባዎች ጭምር ሰላይ በማስቀመጥ ባለስልጣናትን ያሰልሉ እንደነበር አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ ተናገሩ፡፡

የህወሓት አመራሮች በማዕከላዊ ስበሰባዎች ጭምር ሰላይ ያስቀምጡ ነበር ያሉት አምባሳደር ኩማ፣ ጉንጭ አልፋና ተጠያቂነት የሌላቸው ስብሰባዎች ይበዙ እንደነበር እና ኦህዴድ በተገመገሙ አመራሮች እርምጃ ሲወስድ ጣልቃ በመግባት ይረብሹ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
የህወሓት ዘራፊ ቡድን የቁልቁለት ጉዞን የጀመረው በ1993 ዓ.ም መሆኑንም አምባሳደር ኩማ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስታውሰዋል፡፡
በ1983 ዓ.ም ወደ ስልጣን የመጣው ኢህአዴግ በህወሓት መሪነት ሶስት መሰረታዊ አላማዎችን አንግቦ መንገዱን ጀመሯል የሚሉት አምባሳደሩ፣ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ዴሞክራሲና ልማት ማረጋገጥ የቤት ስራው መሆኑን አስቀምጦ ሀገር መምራት ቢጀምርም ግልጽ የሆነ የርዕዮትዓለም ሳይኖረው ለአስር ዓመታት በጭፍን ሲጓዝ ነበር ብለዋል፡፡
ከ10 አመታት በኋላ በ1993 ዓ.ም ሰነዶች ተዘጋጅተው ለውይይት እንደቀረቡ ገልጸው፣ የውይይት ሃሳቡና ኢህአዴግ የሚመራበት ሰነድ በህወሓት ቡድኖች መሃል የልዩነት መስመር ማበጀቱን ጠቁመዋል፡፡
ዴሞክራሲን በሰነድ ከማስፈር ውጪ በተግባር የማያውቀው ህወሓት በሀገሪቱ ዴሞክራሲ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል አምባሳደር ኩማ፡፡ ይህ ደግሞ ውድቀቱን አፋጥኖታል፤ ሌሎችም ፓርቲዎችም ከህወሓት ውደቀት ሊማሩ ይገባል ብለዋል፡፡
(በአካሉ ጴጥሮስ)