የህዳሴ ግድብ ሙሌትን ለመደገፍ ለሀምሌ 16 ታቅዶ የነበረው ህዝባዊ ሰልፍ ተራዘመ

ኢሳያስ አለማየሁ

ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) – የህዳሴ ግድብ ሙሌትን ለመደገፍና የውጪ ጫናን ለመቃወም በሚል ለሀምሌ 16 ታቅዶ የነበረው ህዝባዊ ሰልፍ ወደ ሀምሌ 25 መራዘሙ ተገለጸ።

የዩዝ ኔትወርክ ሰስቴኔብል ዴቨሎፕመንት ዋና ዳይሬክተር ኢሳያስ አለማየሁ አዘጋጆቹ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ምክክር በመግባባታቸው እንደሆነ ለዋልታ ገልፀዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ5 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ይሳተፉበታል ተብሎ የተገመተው ትዕይንተ ህዝብ ሀምሌ 16 አመሻሽ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሰልፉ እንዲራዘም መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ሀምሌ 15 በአዲስ አበባ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለህዳሴ ግድብ የድጋፍ ሰልፍ መካሄዱን አስታውሰው፣ ፕሮግራሞች በቀዳሚው ሰልፍ በመዋጥ መተላለፍ የሚገባው መልዕክት ሳይተላለፍ እንዳይቀር በሚል ሰልፉ እንደተራዘመም በምክንያታዊነት ጠቁመዋል፡፡

ወጣቱን በተከታታይ ቀን ስራ አስትቶ ለሰልፍ ማስወጣቱ መሰላቸት እንዳይፈጥርና እንዲሁም የፀጥታ አካላት የሚኖረውን የስራ መደራረብ ለመቀነስ ሲባል ማራዘሙ አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል።

በመሆኑም ለህዳሴ ግድብ የሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ በመጪው ሀምሌ 25 ከጠዋቱ 2:30 እስከ 5:00 ሰዓት እንዲካሄድ ተወስኗል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

 

ሰላማዊ ሰልፉ በዩዝ ኔትወርክ ሰስቴኔብል ዴቬሎፕመንት፣ በሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ በሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የሚዘጋጅ ነው።

(በሱራፌል መንግስቴ)