የህገ- መንግስት አጣሪ ጉባኤ እጩ አባላት እንዲሾሙ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ጸደቀ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት እያካሄደ በሚገኘው ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባ የህገ- መንግስት አጣሪ ጉባኤ እጩ አባላት እንዲሾሙ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ጸድቋል።

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 ፊደል ተራ ቁጥር “ሐ” መሰረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት የሚሾሙ በሙያ ብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሾሙ ይታወቃል።

በህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ቀደም ሲል የተመረጡት አባላት የአገልግሎት ጊዜያቸው በሐምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ተጠናቋል።

በመሆኑም በምክር ቤቱ በሙያ ብቃታቸው እና በስራ ልምዳቸው የቀረቡት እጩዎች በሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት የሚሾሙ በመሆኑ በዛሬው እለት በ4 ተቃውሞ በ12 ድምጸ ተዓቀቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የህገ መንግስት አጠሪ ጉባኤ 11 አባላት ሲሆኑ 6ቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ ናቸው።

በህገ – መንገስቱ አንቀጽ 82 እንደተቀመጠው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አሥራ አንድ አባላት ይኖሩታል፡፡

ጉባኤውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በሰብሳቢነት እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት በምክትል ሰብሳቢነት ይመሩታል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት የሚሾሙ በሙያ ብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የሕግ ባለሙያዎችም ይኖሩታል።

ምክር ቤቱ እያካሄደ በሚገኘው መደበኛ ስብሳበው ለፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባልነት የቀረቡለትን ዕጩ የጉባኤ አባላት በ13 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ኢዜአ እንደዘገበው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራ ይጠበቃል።