የህግ ማስከበር እና መልሶ ግንባታ ሂደትን የሚያፋጥን ውይይት ተካሄደ

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሰላም፣ የህግ ማስከበር እና መልሶ ግንባታ ሂደትን ለማፋጠን የሚያስችል ሀገር አቀፍ ውይይት ተካሄደ፡፡

በስትራቴጂክ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የተዘጋጀው ሀገር አቀፍ የውይይት መድረኩ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እና ተቋማትን መገንባት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በውይይት መድረኩም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ምሁራን እና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የስትራቴጅክ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ቧያለው ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቱን የሰላም እና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት በማድረግ የምርምር ስራዎችን እና አማራጭ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን የሚያቀርብ እንደሆነ ጠቁመው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋት የሚረዳ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በሰላም እና መልሶ ግንባታ ምዕራፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንዲሁም ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም አቶ ዮሃንስ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ በሰላም እና መልሶ ግንባታ ምዕራፍን በተመለከተ ሶስት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ላይም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም እና በቀጣይነትም አስተማማኝ ተቋማትን መገንባት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንደሆኑ ተነስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ይበልጥ እንዲጎለብት መንግስት ከሚሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ ህብረተሰቡ የራሱን ሰላም መጠበቅ እና የቆየ አብሮ የመኖር እሴቱን ማጎልበት እንደሚጠበቅበትም ተጠቁሟል፡፡

 

የስትራቴጅክ ጉዳዮች ኢኒስቲትዩት በቀጣይም በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት እና የሰላም ግንባታን የሚያግዙ የግንዛቤ እና የክህሎት ማጎልበቻ ስልጠናዎችን እና አማራጭ ምክር ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

(በሜሮን መስፍን)