የህግ ማሻሻያዎችን በአንድ ላይ አካቶ የያዘ መጽሐፍ ተመረቀ

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዚያት የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎችን በአንድ ላይ አካቶ የያዘ መጽሐፍ ተመርቋል፡፡

የመጽሐፉ አዘጋጅ ዶ/ር ኤልያስ ኑር በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የህግ ማሻሻያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመው፣ እነዚህ ህጎች ተበታትነው እንዳይቀሩ በአንድ ላይ ይሰነዱ በሚል ሃሳብ መጽሃፉን አዘጋጅተዋል፡፡

መጽሃፉ በአራት ዋና ዋና ክፍሎች የተደለደለ ሲሆን በመጀመሪያው እትም ሁለቱ ክፍሎች መካተታቸውን አዘጋጁ ጠቁመው፣ ቀሪዎቹ ሁለት ክፍሎች በቅርቡ ለህትመት ይበቃሉ ብለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ገለታ ስዩም በበኩላቸው ጠቅላይ አቃቢ ህግ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በፌደራል መንግስት የሚወጡ ህጎችን ረቂቅ ማዘጋጀት አንዱ እና ዋናው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ መጽሐፍ በዘርፉ ጥናት እና ምርምር ለሚያደርጉ አካላት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ገልጸዋል፡፡

መጽሐፉ በዩኤስአይዲ ፍትህ አክቲቪስት ኢትዮጵያ እና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን ርክክቡም በገለታ ስዩም እና በፍትህ አክቲቪስት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ዴጊል መካከል ተከናውኗል፡፡

መጽሐፉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን ወደ አማርኛ ለመተርጎም ስራዎች ተጀምረዋል፡፡

(በነስረዲን ኑሩ)