የላሙ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – የላሙ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ተገለጸ፡፡

የወደቡ ለአገልግሎት ክፍት መሆን ኢትዮጵያ ለወጪና ገቢ ንግዷ ለወደብ ኪራይ የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ እንደሚቀንስ የታመነበት መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለዘመናት የቆየውን ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በኢኮኖሚው ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት አምባሳደር መለስ፣ አገራቱ በንግድና ኢንቨስትመንት መተሳሰራቸው የህዝቦቹን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል፡፡

የኬንያ የወደቦች ባለሥልጣን ዋና ኃላፊ ኢንጂነር አብዱላሂ ሰመተር በበኩላቸው፣ ከፊል ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት በሆነው የላሙ ወደብን ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ተጠቅመው የንግድ ሥራቸውን እንዲያቀላጥፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኃላፊው የላሙ ወደብን ለጎበኘው የኢትዮጵያ የሚዲያ ቡድን እንደገለጹት፣ ተጨማሪ ሁለት የመርከብ ማቆያ ግንባታ በቅርቡ ይጠናቀቃል። አሁን ላይ አጠቃላይ የወደቡ የግንባታ ሂደት 90 በመቶ መጠናቀቁም አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በወደቡ መርከቦቿ የሚያርፉበት ቦታ እየተዘጋጋ እንዳለ የተገለፀ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ረጅም ጊዜ የሚፈጀውንና ለከፍተኛ ወጪ የሚዳረጉበትን የወደብ ክፍያ በመቀነስ በጥቂት ቀናት ብቻ ወጪና ገቢ ንግዳቸውን ማቀላጠፍ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

የላሙ ወደብን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለምን ጨምሮ ዲፕሎማቶች፣ የላሙ ግዛት አስተዳዳሪዎች እና የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጎብኝተዋል፡፡

(በአስታርቃቸው ወልዴ)