የሕዝብን ደኅንነት በማረጋገጥ ልማትን ማስቀጠል እንዲቻል በተደራጀ ዕቅድ መመራት እንደሚገባ ተገለጸ

መጋቢት 30/2014 (ዋልታ) በክልሉ ሰላምና የሕዝቦችን ደኅንነት በማረጋገጥ ልማትና ዕድገትን ማስቀጠል እንዲቻል ወጥነት ባለው አሰራርና በተደራጀ ዕቅድ መመራት አለብን ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሠ መስተዳድር ሽመለስ አብዲሳ ገለጹ።
የክልሉ መንግሥት የ2014 የሶስተኛ ሩብ በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ሲሆን ርዕሠ መስተዳድሩ የክልሉ ሰላም፣ ፀጥታና የሕዝቦችን ደህንነት በማረጋገጥ ልማትና ዕድገትን ለማስቀጠል ወጥነት ባለው አሰራርና በተናበበ ዕቅድ መመራት አለብን ብለዋል።
ወቅታዊውን የፀጥታ ሁኔታ፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር እጦትን አንስተዋል።
እንዲሁም የ2015 በጀት ዓመት የክልሉ የልማት ዕቅድ፣ የኑሮ ወድነት፣ የወጣቶች የሥራ አጥነት ደግሞ በመድረኩ ትኩረት የሚሰጣቸውና ቀጣይ የአፈፃፀም ተለይተው አቅጣጫ እንደሚሰጥባቸው ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት ክንውኑ በተቀመጠው እቅድ ልክ ስለመሆኑ፣ አቅጣጫና አሰራሩ ተጠብቆ ስለመካሄዱ፣ በአፈጻጸም ሂደቱ የነበረው ቁርጠኝነት፣ የታዩ ክፍተቶችና ችግሮችን ለመፍታት በተለይም ሕዝቡን ከማሳተፍና የሃብት ብክነትን ከመቀነስ አንጻር ያለው ሁኔታ በመድረኩ እንደሚገመገም አስታውቀዋል።
እንደኢዜአ ዘገባ ሌብነትን ከመከላከልና በሕዝባዊ መድረኩ የተነሱ ጉዳዮች በባለቤትነት ከመፈፀምና ከማስፈፀም አንፃር በትክክል ፈትሸን ቀጣይ አቅጣጫ እናስቀምጣለን ሲሉ ርዕሠ መስተዳድሩ አብራርተዋል።