የሕገ መንግስት ማሻሻያ ጥያቄዎች በአግባቡ ሊታዩ ይገባል- የፌደሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ

የሕገ መንግስት ማሻሻያ ጥያቄዎች በአግባቡ ሊታዩ እንደሚገባ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር የግምገማ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ሕገ መንግስቱ በጸደቀበት ቀን የምናከብረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ህዝቡ ስለህገ መንግስት የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኝ እንደመልካም አጋጣሚ እንጠቀምበታለን ብለዋል፡፡

የሕገ መንግስት ማሻሻያ ጥያቄዎች በአግባቡ ሊታዩ ይገባል ያሉት አፈ ጉባኤው፣ በሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ፍላጎት ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚችል በመድረኩ ላይ አንስተዋል፡፡

ከማሻሻያ በፊት ዕውቀት አስፈላጊ ስለሆነ ስለ ሕገ መንግስቱ ግንዛቤ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት አቶ አደም፣ ከግንዛቤው ባለፈም ሕገ መንግስቱን ማክበር ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሶስት ዋና ዋና ዓላማዎች የሚከበር መሆኑን ያነሱት አፈጉባኤው፣ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራቱን በመግለፅ፤ ከሴቶች፣ ወጣቶች፣ ልሂቃን እና መንግስት ሰራተኞች ጋር በሕገ መንግስቱ ዙሪያ ውይይት መካሄዱን አመልከተዋል፡፡

የዳበረ ዴሞክራሲ ያላትን ሀገር ከመፍጠር አንፃር የወጣቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነና ወጣቱ ልዩነት እንኳን ቢኖር ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የትግል አቅጣጫን እንዲከተል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያን የሚመስሉ ተቋማትን መፍጠር ለአገረ መንግስት ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡

ከግንዛቤ ማስጨበጥ ባለፈ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ማስቻልና የራሳቸውንም ባህል ማስተዋወቅ እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦች ትስስርና አንድነትን ማጠናከር የበዓሉ ሌላኛው ዓላማ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በግምገማ መድረኩ ባለፉት ዓመታት ብሔር ብሔረሰቡን የሚለያዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሰራ መቆየቱ የተነሳ ሲሆን፣ የዘንድሮው በዓል ምንም እንኳን በፈታኝ ሁኔታዎች የታጀበ ቢሆንም፣ ፈታኝ ሁኔታዎች ተቋቁሞ ዋጋ የሚሰጠው ተግባር መከናወኑ ተነስቷል፡፡

15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከዚህ ቀደም ከነበረበት የፖለቲከኞች በዓልነት ወደ ህዝብ በዓልነት ለመቀየር የተሰራበት እንደሆነም ከተሳታፊዎች ተነስቷል፡፡

በቀጣይ በአገሪቱ እየተስፋፉ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የማይገልፁ ግጭቶችን መፍትሔ መስጠት ወሳኝ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከዚህ ባለፈ በዓሉ ሲከበር አንዱ ብሔር የሌላውን ብሔር አቅፎ በመያዝ አብሮነቱን በማጠናከሩ ማበረታቻ ሊበረከትለት ይገባል ተብሏል፡፡

በመድረኮች ብቻ ለውጥ ማምጣት ስለማይቻል በመሬት ላይ የሚተገበር ቀመር አስፈላጊ መሆኑንም የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡

ትኩረት ተነፍጎት የቆየውን ሲቪል ሰርቪሱን ከምርኮኝነት በመፍታት፤ ሲቪል ሰርቪሱ በብሔር ብሔረሰቦች የኢኮኖሚ፣ የማህበረሰብ፣ የባህል መብቶች የሚጫወተውን ሚና ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል፡፡

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “እኩልነትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች መከበሩ ይታወሳል፡፡

(በሳሙኤል ሀጎስ)