የመርከቦችን የወደብ ቆይታ ከነበረበት 12 ቀናት ወደ 9 ቀናት ለመቀነስ ተችሏል

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመርከቦችን የወደብ ቆይታ ከነበረበት 12 ቀናት ወደ 9 ቀናት ለመቀመስ መቻሉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሰታወቀ።
ሚኒስቴሩ የተጠሪ ተቋማቱን 2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ ገምግሟል።
የኤክስፖርት ምርቶችን በኮንቴነር አሽጎ ከመላክ አንጻር አፈፃፀሙን በማሻሻል ድርሻውን ወደ 62 ነጥብ 5 በመቶ ማድረስ እንደተቻለና አንድ ነጥብ 34 ሚሊየን ቶን ካርጎ በባቡር ማጓጓዝ መቻሉን በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በዘርፉ ለ71 ሺሕ 300 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ62 ሺሕ 420 ጎጎች የሥራ እድል ተፈጥሯልም ነው የተባለው።
የፐብሊክ ሰርቪስ የትራንስፖር አገልግሎት ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች የሚሰጠውን አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡
በአቪየሽን ዘርፍ ለማሳካት የታቀደውን የብቃት ማረጋገጫ የመስጠት አገልግሎት ማሳካት የተቻለ ሲሆን የበረራ ደኅንነትን ከዓለም ዐቀፍ ደረጃ አንጻር አስጠብቆ ለማስኬድ ተችሏል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ለተሻለ ውጤት በትብብርና በቅንጅት የመስራት ባህልን ይበልጥ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ሁሉም ተቋማት የተሻለ አፈፃፀም እንዳላቸውም ጠቁመው ቀሪውን 3 ወራት በአግባቡ መጠቀምና የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሁሉም ተቋማት ከወረቀት የፀዳ የድጅታይዝ አሰራር መከተል እንዳለባቸው በመጠቆም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።