የመሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ ምርቱን ለገበያ ማቅረብ ጀመረ

መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – በህግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት ባለፉት አራት ወራት ስራ አቁሞ የነበረው ትግራይ ክልል የሚገኘው መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ የማምረት ስራውን በመጀመር ምርቱን ለገበያ እያቀረበ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

በህገ-ወጥ ደላሎች የምርት መሰወር ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የአንድ ኩንታል የሲሚንቶ ዋጋ አስከ 6 መቶ ብር ደርሶ የነበረ መሆኑን እንደማሳያ የገለፁት ሚኒስትሩ፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በተሰራው ጥብቅ የቁጥጥርና ክትትል ስራ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ የመሸጫ ዋጋ ወደ 420 ብር ቀንሷል ብለዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች የምርት መጠናቸውን በመጨመር በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሲሚንቶን ምርት የመሸጫ ዋጋ ተመጣጣኝ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ  አበረታች ውጤት ማምጣቱን የገለፁት አቶ መላኩ፣ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለማስተካከል በከፍተኛ ትኩረት የድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መሰቦ ሲሚንቶ ወደ ማምረት በመመለስ ምርቱን ለገበያ ማቅረብ መጀመሩ ለዋጋ መሻሻሉ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለዘርፉ የዋጋ መሻሻል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሀገራዊ ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡