የመስቀል ደመራ እና የመውሊድ በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸው ተገለጸ


መስከረም 16/2016 (አዲስ ዋልታ) በዛሬው ዕለት በመላ ሀገሪቱ የተከበሩ የመስቀል ደመራ እና የመውሊድ በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።

የጋራ ግብረ-ኃይሉ ቅደመ ዝግጅት በማድረግ የአዝማሚያ ትንተና በማካሄድ ተጋላጭ ቦታዎችንና አካባቢዎችን ለይቶ በቅድመ መከላከል ሥራው ላይ በርካታ የሰው ኃይል በማሰማራት እና ለሥራው አጋዥ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከህዝቡ፣ ከሁለቱ የእምነት ተቋማት የሃይማኖት አባቶች፣ ከበዓላቱ አዘጋጅ ኮሚቴዎችና ከወጣቶች ጋር ተባብሮ በመስራቱ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሁለቱም በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን ባወጣው መግለቻ አመልክቷል፡፡

በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረገው ህዝባችን እንዲሁም የሀይማኖት አባቶች፣ ለበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እና ለወጣቶች የጋራ ግብረ ኃይሉ ላቅ ያለ ምስጋና ያቀርባል ብሏል በመግለጫው።

የፀጥታና ደህንነት ኃይሎችም የተሰጣቸውን ግዳጅ በሚገባ ስለተወጡ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡

ህብረተሰቡ እንደተለመደው የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ እያሳየ ያለውን ቀና ትብብር ወደፊት በሚከበሩ ሌሎች ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ላይም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡