የመከላከያ ሚኒስትሩ ከሱዳን ጋር ተቀራርበን መሥራት እንደሚገባን መግባባት ላይ ደርሰናል አሉ

ጥር 15/2014 (ዋልታ) ከሱዳን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን መሥራት እንደሚገባን መግባባት ላይ ደርሰናል ሲሉ የአገር መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ወደ አገራቸው ሲመለሱ የመከላከያ ሚኒስትሩ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።

የጄነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን የኢትዮጵያ ቆይታ በተመለከተ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያና በሱዳን የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል።

“አብረንና ተቀራርበን መሥራት እንደሚገባን ተግባብተናል” ሲሉም ገልጸዋል።

ትናንት አዲስ አበባ የገቡት ጄነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል።

ጄነራሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ከአገር መከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና ከኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።