የመከላከያ ሰራዊት ከትናንት ጀምሮ መውሰድ በጀመረው ጠንካራ እርምጃ አስተማሪ ሥራ እየሰራ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) የመከላከያ ሰራዊት ከትናንት ጀምሮ መውሰድ በጀመረው ጠንካራ እርምጃ የጠላት ተላላኪዎችን ሊያስተምር የሚችል ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ እርምጃ አየተወሰደ የሚገኘው የት እንደሆነ ባይገልጹም ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በተፈጸመ ብሔር ተኮር ጥቃት በፈጸመው ኦነግ ሼኔ ላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

በጥቃቱ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በሽብርተናው አማጺ ቡድን መገደላቸውን እና በሺሕዎች የሚቆጠሩ ደግሞ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት አራተኛውን ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ የእጽዋት ማዕከል ዛሬ በይፋ ሲያጀምሩ ነው፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ከኢትጵያውያን የሚጠበቀው ሀገራችንን መንከባከብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንከባከብ ሲባል ሀገር ምድር ብቻም ሳይሆን ሰውንም ጭምር ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ ከወታደር እና ከፖሊስ ጋር በቀጥታ መግጠም የማይችሉ ተላላኪ ባንዳዎች ንፁሃን ኢትዮጵውያንን ይጨፈጭፋሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ጸያፍ ድርጊት ለማስቆም ሁሉም ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው በአፅንዖት ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ ንፁሃን ኢትዮጵያውያን መኖር የማይችሉበት ምድር ለማድረግ እና የያዝናቸውን መልካም ሃሳቦች ለማጨናገፍ የሚሞክሩ ኃይሎችና ተላላኪዎቻቸው ትልሞቻቸው እንዳይሳካም መከፋፈል ሳይሆን ሰብሰብ ብለን በተደመረ ክንድ ጠላቶቻችንን ማሳፈር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

“ዜጎቻችንን የጨፈጨፉትንም በህግ አግባብ ማስተማር ይጠበቅብናል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልክታቸውን አክለዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር ከትናንት ጀምሮ መውሰድ በጀመረው ኦፕሬሽን ጠንካራ የማስተማሪያ ሥራ እየሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉዳዩ የሁሉንም አመራር ትኩረት እንደሚሻ አስምረውበታል፡፡

“በቀኝ እጃችን ልማታችንን እናስቀጥላለን፤ በግራ እጃችን ደግሞ ጠላቶቻችንን እንዋጋለን፣ የሚቆም ነገር የለም” ሲሉ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW